
በአንድ ወቅት እንደዚህ ነበር የሰው ኑሮ
ሰው ነገን ለማየት ዛሬውን ተሻግሮ
ቀኑን አጠናቆ ሲደርስ ከወደቡ
መሳፈር አለበት ከነገ መርክቡ
የዚህ ጉዳይ መሪ ስም ዝርዝር አውጥተው
ከመርከበኞቹ አንድ አስሩን ጥርተው
አሻግረው ሲያበቁ የተመረጡትን
ለፍርድ ያቀርባሉ ያልተሻገሩትን
የኔም ተራ ደርሶ ..........
የሂወትን ጉዞ '' ሀ '' ብዬ ጀምሬ
በዛሬ መርከብ ላይ ስሄድ ተሳፍሬ
ደርሶብኝ አልፌ ብዙ አይነት መከራ
አቤት እሚል ጠፍቶ በሲቃ ስጣራ
በሰዎች ጭካኔ አርባ ተገርፌ
አለም ተፀይፋኝ እጅግ ተነቅፌ
የእኔ መልካም ስራ የሚታየው ጠፍቶ
ስሜ በሀገሩ ላይ ቆሽሾ ከርፍቶ
" እኔ እሱን ቢያደርገኝ፣
በስሙኒ ገመድ ተንጥልጥዬ ልገኝ"
ሲሉኝ እሰማለሁ፤ ግን ለምን ሞታለሁ
በፈጣሪ ስራ እጄን አስገባለሁ
እያልኩ ስሟገት ከሀሳቤ ጋራ
ወደብ ላይ ደረስን ስማችን ሊጠራ
ሊያበቃ ነውና የዛሬያችን ጉዞ
አንድ ሰው ብቅ አለ ትልቅ መዝገብ ይዞ
በፅሞና አዳምጡ እዚህ እምትወርዱ
ከተማ፣ ከበደ፤ አበራሽ፣ ስንዱ
ቀጠለና ጠራ አስር ሰው ቀነሰ
በመላ አካላቴ ፍርህት ነገሰ
ዛሬ ሰልችቶኛል ጉዞው አድክሞኛል
ተስፋ የጣልኩበት ነገዬ ናፍቆኛል
እያልኩ ስናውዝ ውስጤ ተመሳቅሎ
ስሜ ተጠራና ተስፋሁን ተብሎ
አምላክ ቀላቅለኝ ከነገዎች ጎራ
ዛሬዬን አፍርሶ ነገዬን ሊሰራ
ከዚያ ሁላችንም በትንሿ ጀልባ
ከዛሬ ላይ ወርደን ከነገ ስንገባ
ከተሳፈርንባት ከቀድሞዋ መርከብ
"ዛሬ" እሚለው ጥፍቶ "ትናንት" ሲከተብ
የተሳፈርናቱ የነገዋ ጀልባ
ዛሬ ተፅፎባት አምራ እና ተውባ
ጉዞዋን ቀጠለች በፍቅር ታጅባ
ይህን ግዜ ታድያ ነፍሴ ነፍስ ዘርታ
የትናንት መከራ ስቃይዋን ረስታ
ተአምራዊ ለውጥ በሂወቴ ሆነ
ስቃይ ጉስቁልና እንደ ጉም በነነ
አዲስ ቀን ተችሮኝ ነገር ተቀይረ
የእስራት ቀንበሬም ይሄው ተሰበረ
በሂወት ስንኖር ሀዘን እና ደስታ
የትንሿ ሳንቲም ሁልት ገፅታ
መሆኗን ተረዳሁ ስነቃ ከህልሜ
ትናንትን እያሰብኩ ዛሬዬ ላይ ቆሜ፡፡
https://www.tiktok.com/@derudreams/video/7540050790757567749?is_from_webapp=1&sender_device=pc
